News Single
Explore our peace-building initiatives and success stories on
achieving global peace through community unity on our Global Peace
Bank Blog.
Explore our peace-building initiatives and success stories on
achieving global peace through community unity on our Global Peace
Bank Blog.
ዳያሞ ዳሌ ዳጋ (የግሎባል ፒስ ባንክ የሰላም ግንባታ እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር)--
ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም
ዛሬ በአውሮፓዊው የዘመን አቆጣጠር ሜይ 25 ቀን 2025 ዓ.ም ነው። ከ62 ዓመታት በፊት በዛሬው ዕለት ፣ ሜይ 25 ቀን 1963 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚባል አህጉራዊ ድርጅት የተመሰረተ በመሆኑ ዕለቱን "የአፍሪካ ቀን" (Africa Day) ብለን እያከበርነው ነው። ድርጅቱ የተመሰረተው ዋና ጽሕፈት ቤቱን በአገራችን ዋና ከተማ፣ አዲስ አበባ አድርጎ በመሆኑ ኢትዮጵያ አገራችን የአፍሪካ-አቀፍ ሁለገብ ዕንቅስቃሴ ማዕከል ነች።
አፍሪካዊያን ከአውሮፓዊያኑ ሀይሎች ቅኝ አገዛዝ ነጻ መውጣት የጀመሩት በ1950ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ነው። ከዚያ ቀደም በነጻ አገረ መንግሥትነት የነበረችው አፍሪካዊት አገር አገራችን ኢትዮጵያ ነች- በአሜሪካ የባሪያ ነጻነት ከታወጀ በኋላ ከባርነት ነጻ የወጡ ጥቁሮች የመሠረቷት ላይቤሪያ መኖሯ እንደተጠበቀ ሆኖ።
የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ገዥዎች የተያዙበት እና የተገዙበት ሥርዓት በሰው ልጅ እኩልነት የማያምን ዘረኝነት እና ዘራፊነት የተቀላቀለበት የዐመፅ አገዛዝ ሥርዓት ስለነበር፣ ከዚያ ሥርዓት አርነት ለመውጣት የተደረገው ትግልም ዐመፅን መሣሪያ ያደረገ የተቃውሞ ስልት ሆኗል። አልጄሪያን በመሳሰሉ አገሮች ለአገራዊ ነጻነት የተደረገው ተጋድሎ የሚሊዮኖችን ሕይወት የቀጠፈ የተራዘመ የትጥቅ ተጋድሎ ነበር።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንደተመሰረተ ቀዳሚ ዓላማ ያደረገውም ከቅኝ ግዛት ነጻ ያልወጡ አፍሪካዊያን ነጻ እንዲወጡ ኦፊሴላዊ ድጋፍ መስጠትን ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ የተመሠረተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን ሕገወጥ ሥርዓት አድርጎ የፈረጀ ቢሆንም፣ ቅኝ ገዥ አገሮች ቅኝ ግዛቶቻቸውን በቀላሉ ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልነበሩም። በአፍሪካ ውስጥ፣ በተለይ ፖርቹጋል ሞዛምቢክን፣ አንጎላን፣ ጊኒ ቢሳውን የመሳሰሉ ሀብታም ቅኝ ግዛቶቿን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኗ የእነዚህ ቅኝ ግዛቶች ሕዝቦች የሚያካሂዱትን ደም አፋሳሽ የነጻነት ትግል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ደግፎ ለድል በቅተዋል። የታላቋ ብሪታኒያ ቅኝ ግዛቶች ከነበሩት መካከል ሮዴዢያ (የዛሬዋ ዚምባቡዌ) እና ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ከቅኝ ገዥዋ "ነጻ ወጥተናል" ባሉ የግዛቶቹ ጥቂት ነጭ ሰፋሪዎች የተመሠረቱ የዘር ክፍፍል (አፓርታይድ) ሥርዓት ጥቁሮችን ከሰው በታች አድርገው ማሰቃየት በመቀጠላቸው የግዛቶቹ ነዋሪ ጥቁሮች የተራዘመ የትጥቅ ትግል ለማድረግ ተገደዋል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይህንኑ ትግል እስከ 1994 የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ ደግፏል።
"የአፍሪካ ህብረት ከተመሰረተ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ የወጡት አፍሪካዊያን የሚኖሩት ሕይወት ምን ይመስላል?" ብለን ስንጠይቅ፣ የምናገኘው ምላሽ አሳዛኝ ነው። የአፍሪካ ድህነት እና የአፍሪካ ኋላቀርነት የተፈጥሮ ሕግ ወይም የእግዚአብሔር ልዩ ውሳኔ እስኪመስል ድረስ የማይቀየር ዕውነታ ተደርጎ ተወስዷል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የተካው የአፍሪካ ህብረት ከቅኝ አገዛዝ አፍሪካን ነጻ የማውጣት ተልዕኮ ተሳክቶ አፍሪካዊያን ለአዲስ ራዕይ የሚተባበሩት እና የሚቀናጁበት አህጉራዊ ድርጅት ቢሆንም፣ የድርጅቱ የእስካሁን አፈጻጸም የሚያኮራ አይደለም። ዛሬም አፍሪካን ከሁሉም አህጉራት በባሰ ሁኔታ ድህነት እና ኋላቀርነት ጠፍሮ ይዟታል። የአፍሪካ ወጣቶች እና ምሁራን ከአህጉሪቱ በገፍ ይሰደዳሉ። የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ብቻ ሳይሆን፣ ሳይከሰትም አፍሪካዊያን ለተረጂነት ተዳርገዋል። የሁሉም የአፍሪካ ችግሮች መንስኤ የሰላም ዕጦት ነው።
በነዳጅ ሀብት የታደለችው እና ከአፍሪካ አገሮች በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ የሆነችው ናይጄሪያ፣ ከነጻነቷ በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እና በሀይማኖታዊ ጽንፈኝነት ዐመጾች ትንፋሽ አጥታ እየተናጠች ነው። አልማዝ፣ ወርቅ፣ ታንታለም፣ ኮባልት እና በዚህ ዓለም ውድ የሆነውን የማዕድን ዓይነት ሁሉ በከርሷ ያቀፈችው ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዜጎቿ በዐማጽያን ፍጅት የሚያልቁባት እና የሚሰደዱባት የምድር ሲኦል ነች። የአፍሪቃ ቀንድ በሚባለው ንዑስ-ንዑስ አህጉር የሚገኙት ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ ወይ ከውጪ-ከጎረቤት፣ ወይ ከውስጥ፣ ወይም ከሁለቱም በሚለኮሱ ዐመጾች ሰላምን ተነፍገው የሚሰቃዩ አገሮች ናቸው።
"በዐረብ ጸደይ" ስም በተቀጣጠለው ረብሽ ከፈራረሰችው ሊቢያ እና አል ቃይዳን በመሳሰሉ ድንበር-የለሽ አክራሪ ንቅናቄዎች ከሚያምሷቸው የሰሜን አፍሪካ አገሮች አንስቶ የእርስ በርስ ጦርነት እና የአክራሪነት ሁከት የሚበጠብጣቸውን ሞዛምቢክን ከመሳሰሉ ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች ድረስ አፍሪካን "የሚያስተሳስረው" አንዱ ዕውነታ የሰላም ዕጦት ነው።
የአፍሪካ ህብረት ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቶኛ ዓመት ለማሳካት በነደፈው "አጀንዳ 2063" የያዘው ራዕይ "በ2063 ሰላሟ የተሟላ፣ የበለጸገች እና የተዋኻደች አፍሪካን መፍጠር" የሚል ነው። በ2013 የጸደቀው "አጀንዳ 2063" ራዕዩ እንዲሳካ ከያዛቸው ግቦች ቀዳሚው "በ2020 ጠብመንጃን ጸጥ ማድረግ" (Silencing the Guns) የሚል ነበር። "ጠብመንጃን ጸጥ ማድረግ" የአፍሪካ አህጉርን ከእርስ በርስ ጦርነቶች፣ ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከሚያደርሱት ውድመት፣ ከጾታዊ ጥቃቶች እና ከዘር ማጥፋት ወንጀሎች ሁሉ ነጻ ማድረግ ማለት ነው። ዛሬ 2025 ዓ.ም ነው። በአፍሪካ አህጉር ጠብመንጃ ጸጥ ሊደረግ አልቻለም። እንዲያውም የጠብመንጃ አፍ በደንብ እንዲከፈት፣ ዐመፅ እንዲስፋፋ፣ ሁከት እንዲባባስ የሚገፋፉ አንደበቶች እና ተግባራት እየበዙ ነው።
በዚህ ሁኔታ የአፍሪካዊያን ተስፋ እየጨለመ፣ የሁከት እና የዐመፅ አዙሪት እየጠነከረ ይሄዳል።
በጦርነት ባህል እና ልማድ የተጠመደ ማህበረሰብ እርስ በርስ እየተጠፋፋ፣ የሌሎች የበታች እና ለማኝ የመሆን ዕድል እንጂ፣ በባህሉ ስሜት ውስጥ ሆነን እንደምናስበው የጀግንነት ባለቤት እንደማይሆን የአፍሪካ ማህበረሰብ በቂ ማሳያ ነው። እኛ፣ እንደ ግሎባል ፒስ ባንክ፣ ይህ ባህል መቆሙ የሕልውና ዋስትና ነው ብለን እናምናለን። በጦርነት እና በዓመፅ ልማድ ውስጥ በተዘፈቀ ማህበረሰብ የወል ተሸናፊ እንጂ፣ አሸናፊ እና ተሸናፊ ይኖራል ብለን አናምንም። በተለይ ደግሞ፣ በአፍሪካ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ግጭት እንደሚስተዋለው ከጎረቤት ጋር እየተናከሱ፣ ጎረቤትን ሰላም አሳጥቶ የራስን ሰላም የማረጋገጥ ሀሳብ በጭራሽ ሊሳካ የማይችል ሀሳብ መሆኑን በአጽንኦት እናምናለን። አፍሪካዊያን ከዐመጽ አዙሪት ወጥተው ሰላሟ የተሟላ፣ የበለጸገች እና የተዋሀደች አፍሪካን መፍጠር እንዲችሉ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብ፣ በአገር፣ በንዑስ አህጉር፣ እና በአህጉር እርከኖች ሁሉ "ቅድሚያ ለጎረቤት!" በሚል መርህ ባህሪያቸውን እና ግንኙነታቸውን እንዲቃኙ ጥሪ እናቀርባለን!
መልካም የአፍሪካ ቀን!
2025-05-25