blog post

የግሎባል ፒስ ባንክ ሥራ አስኪያጅ አቶ አርጋው አየለ የባኔ ማህበረሰብ የመሪነት ማዕረግ ተሰጣቸው። - ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም (Global Peace Bank News)



የግሎባል ፒስ ባንክ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አርጋው አየለ በባኔ ማህበረሰብ መሪ ፣ ብታ ላሌ እጅ የባኔ ማህበረሰብ መሪነት ሹመት ተቀብለዋል። 

አቶ አርጋው የዋናው መሪ ታናሽ ወንድምነት ዝምድና ደረጃ ተሰጥቷቸው በማህበረሰቡ ዋናው መሪ አማካኝነት የማህበረሰቡን መሪ ሹመት "ብታ" ማዕረግ ይዘው የባኔ ማህበረሰብ አባል እንዲሆኑ መወሰኑ የተገለፀው ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም የባኔ ማህበረሰብ መሪ መኖሪያ በሆነው ቦሪ ቀበሌ በተካሄደው ሥነሥርዓት ላይ ነው።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ደቡብ ኦሞ ዞን፣ በናጸማይ ወረዳ የሚኖረው የባኔ ማህበረሰብ ለአቶ አርጋው አየለ የማህበረሰቡን የመሪነት ማዕረግ ለመስጠት የወሰነበትን ምክንያት በዝርዝር የገለፁት ብታ ላሌ፣ አቶ አርጋው በአብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ደቬሎፕመንት አሶሲዬሽን እና በግሎባል ፒስ ባንክ አማካኝነት የሚያከናውናቸው ተግባራት የአሁኑ የባኔ ማህበረሰብ መሪ አያት የሆኑት ብታ አድነው ጋርሾ ሲያከናውነት የነበረውን ሰብዓዊነታዊ እና የሰላም ግንባታ ተግባራት የሚያስቀጥሉ  ሆነው መወሰዳቸውን አብራርተዋል።

የብታ ላሌ አያት፣ ብታ አድነው ጋርሾ በባኔ ማህበረሰብ ሕጻናት ላይ "ሚንጊ" በሚባለው የማህበረሰቡ ልማድ ሲፈጸም የነበረውን ጎጂ ተግባራት በማስቆም በአካባቢው ማህበረሰቦች ከነበሩ መሪዎች ሁሉ በተለየ ሁኔታ የሚታወሱ መሆኑ በሥነሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

ብታ አድነው ጋርሾ የሚታወቁበት ሌላው ተግባር ከአጎራባቾቹ ማሌ ማህበረሰብ እና ሙርሲ ማህበረሰብ ጋር በማያቋርጥ ሁኔታ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት በዕርቅ ሥነሥርዓት ማስቆማቸው እንደሆነ ተገልጿል። ብታ አድነው በመሪነታቸው ዘመን በባኔ ማህበረሰብ እና በሁለቱ አጎራባች ማህበረሰቦች መካከል የመሠረቱት ዕርቅ እስካሁኑ ትውልድ በማህበረሰቦቹ መካከል ሰላም ጸንቶ እንዲቀጥል ማድረጉን የገለፁት ብታ ላሌ ይህ የአያታቸው ተግባር በአቶ አርጋው አየለ የሚመራው ግሎባል ፒስ ባንክ የሚያራምደው "ቅድሚያ ለጎረቤት" መርህ ትክክል መሆኑን ያረጋገጠ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

በሥነሥርዓቱ ላይ የበናጸማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪን ወክለው የተገኙት የዋና አስተዳዳሪው አማካሪ የተከበሩ አቶ አይኬ ዞምቤ የባኔ ማህበረሰብ ለአቶ አርጋው አየለ የሰጠው የመሪነት ማዕረግ ትልቅ መልዕክት ያለው መሆኑን ገልፀው ከእንግዲህ ወዲህ አቶ አርጋው ከማህበረሰቡ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት በማህበረሰቡ ባህላዊ ዕሴቶች ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን እና አቶ አርጋው በሌሎች ማህበረሰቦች ዘንድ የባኔ ማህበረሰብ አምባሳደር እንደሚሆኑ አብራርተዋል።

አቶ አርጋው በአካባቢው ማህበረሰቦች "ሚንጊ" ተብለው የሚጣሉ ልጆችን ወስደው አሳድገው እና አስተምረው ለተሻለ ሕይወት ማብቃታቸው በተለይ በባኔ ማህበረሰብ ሴቶች ዘንድ ትልቅ ከበሬታ እንዳስገኘላቸው የገለፁት ደግሞ በሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት ወ/ሮ ዋንቴ ዞምቤ ናቸው።

አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ደቬሎፕመንት አሶሲዬሽን የባኔ ማህበረሰብን ጨምሮ ከታችኛው ኦሞ ሸለቆ ማህበረሰቦች በ"ሚንጊ" የሚጣሉ ሕጻናትን ሰብስቦ በማሳደግ እና በማስተማር የሚታወቅ ሲሆን ግሎባል ፒስ ባንክ ማህበር ደግሞ ከነዚሁ ማህበረሰቦች ጋር በባህላዊ የግጭት አፈታት እና የሰላም ግንባታ ዘርፍ ሰፊ የትብብር ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑ ይታወቃል።


  ---ዳያሞ ዳሌ ዳጋ

2025-06-25