blog post

ግሎባል ቲስ ባንክ ገቢው ለበጎ አድራጎት የሚውል የ100 ሺህ ብርየመፅሐፍ ግዢ አደረገ

በዘመዱ ደምስስ 

ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም. 

 #ሀዋሳ፣ ኢትዮጵያ 

ግሎባል ፒስ ባንክ ገቢው በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል የመፅሐፍ ግዢ አደረገ፡፡ የግሎባል ፒስ ባንክ ስራ አስኪያጅ አቶ አርጋው አየለ መፅሐፉ ታትሞ ወደገብያ በዋለበት አዲስ አበባ በመገኘት፣ መፅሐፉን ከፃፉት ክቡር ተስፋየ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ጋር ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ የ100 ሺህ ብር ግዢ ፈፅመዋል፡፡ 

አቶ አርጋው በውይይቱ ወቅት “መፅሐፉ ከአገር በቀል እውቀት፣ ጥበብና ዲሞክራሲ ልምምድ አውድን ማዕከል ያደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የግጭት መፍቻ አማራጭ ሀሳቦችን አጉልቶ የያዘ በመሆኑ፣ ግሎባል ፒስ ባንክም ለሰላም ግምባታ የሚጠቀምበትን በርካታ ሀሳብ የያዘ ጉልህ የዕውቀት ሰነድ ስለሆነ፣ ማሕበራችን በተግባር ለሚሰርፀው የግጭት መፍቻ መንገዶች ትልቅ ግብዓት ይሆናል፤” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ “ከመፅሐፉ ይዘት ባሻገር፣ የሽያጭ ገቢው ሙሉ በሙሉ በጎፋ ዞን ተከስቶ ለነበረው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለደረሰባቸው የሕብረተ-ሰብ ክፍሎች የሚውል በመሆኑና፣ ግሎባል ፒስ ባንክ ከያዘው የሰብዓዊ ድጋፍ እቅድ ጋር የተጣጣመ በመሆኑ ነው፤” ሊሉ አክለዋል፡፡  ሌሎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ባለሀብቶችና ግለሰቦች እንዲህ አይነት የመደጋገፍ ባሕል ማዳበር እንደሚጋባም አሳስበዋል፡፡

አቶ አርጋው አየለ ሲቀጥሉ፣ “አገሪቷ ውስጥ በሳል የታሪክ፣ የዕውቀትና የፖለቲካ ምሁራን ያላት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ሁሉም የድርሻውን ባለው አቅም በመፅሀፍ አድርጎ ለሚቀጥለው ትውልድ ማሸጋገር ቢችል፣ የራሳችንን ችግሮች በአገር በቀል ጥበብና እውቀት ለመፍታት አንቸገርም፤” ሲሉ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ከደራሲው ጋር በነበራቸው የቆይታ ጊዜም፣ የግሎባል ፒስ ባንክን አመሰራረት፣ ዓለማ፣ ርዕይና የወደፊት አቅጣጫ በሰፊው ስለማንሳታቸው፣ እንዲም በጋራ ትብብር ስለሚሰሩ የሰላም ግንባታ ሀሳቦች በጥልቀት ስለማቅረባቸው ተናግረዋል፡፡ 

የመፅሐፉ ደራሲ ክቡር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ “በመፅሐፉ ዝርዝር ይዘት ውስጥ የተካተቱ ርዕሰ-ነገሮች ኢትዮጵያው ዲሞክራሲ ባሕል እየገነባን መሄድ፣ አገራዊ አዎንታዊ የሰላም መንገድ እየሰራን መጓዝ፣ ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ዲሞክራሲና ሰላም የማይነጣጠሉ በመሆናቸውና ግሎባል ፒስ ባንክ በዋናነት የሚሰራው ሰላም ስለሆነ፣ በሀሳብ ዙሪያ ለሚያድርገው የንግግር፣ የውይይትና የሰላም ግንባታ ስራ፣ ከተቋሙ ዓላማ ጋር የሚሄዱ ይዘቶች በመፅሐፉ ውስጥ በርካታ ለግብዓትነት የሚውሉ አማራጮችን ይዟል፤” ብለዋል፡፡

ዲሞክራሲና ሰላም የማይነጣጠሉ በመሆኑና፣ አንዱ ለአንዱ ማገዣ ግብዓት ስለሆነ፣ በሰፊው ሊሰራባቸው ይገባል፤ ሌሎቹም ይዘቶችም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገርም መንገድ ይከፍታል፣ ሲሉ ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡ ለተደረገው ግዢ እና የውይይት ግዜ አመስግነው፣ መልካም የስራ ግዜ ተመኝተዋል፡፡ 

 

Share This Article