News Single
Explore our peace-building initiatives and success stories on
achieving global peace through community unity on our Global Peace
Bank Blog.
Explore our peace-building initiatives and success stories on
achieving global peace through community unity on our Global Peace
Bank Blog.
ለአንድአንዱ፣ “ይታደሉታል እንጂ፣ አይታገሉትም፤” የምትለዋ ብሂል መሬት ቆንጠጣ ታሪክ ትሆናለች፡፡ ለአብዛኛው ጀማ ደግሞ፣ ትግልን መጋፈጥ ግድ ይሆናል፡፡ በመታደልም፣ በመታገልም አገርን የሰሩ፣ ታሪክን የቀየሩ፣ ለትውልድ ትሩፋት፣ ቀን መብራት፣ ማታ እራት የሆኑ ባለታሪኮች እልፍ ቢሆኑም፣ እንደሻለቃ ጳውሎስ ያሉቱ ግን ብርቅም፣ ድንቅም ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ማሕፀነ-ለምለምነት፣ የጀግኖች ፍላቂ ምንጭነት፣ የባለ ብዙ ገድል ባለቤትነነት፣ የእልፍ ገፆች ታሪክ ማህደርነት ከተለካ ደግሞ፣ እንደሻለቃ ጳውሎስ ጌታቸው ናደው ያሉ ባለሟሎች ፈር ቀዳጅነታቸው በራሱ ምርጡ ልኬት ይሆናል፡፡ አገር ያክል ነገር በክንድ ጠብቆ፣ ታሪክን ያክል ቁምነግር በብዕር ሰንዶ፣ ጥበብና ፍልስፍናን ለሕዝብ አጋርቶ፣ እድሜን ኖሮ እንደማረፍ፣ መታደልና መታገልስ በዚህ ዘመን ከየት ይገኛል፡፡
አንድ አንዱ እራሱ ገድል ሆኖ፣ ገድልን ይኖራታል፡፡ የታደለም እራሱ ባለደርዝ ታሪክ ሆኖ፣ ታሪክ ይሰራል፤ ይፅፋል፡፡ ጥበብን ያጠመቀው ደግሞ፣ እራሱ መልከ-ስብዕናው ጥበብ ሆኖ ሳለ፣ ጥበብን ያጋራል፤ ያሻግራል፡፡ ይህ ዕውነት፣ በዘመናት መካከል ያበራ ኮከብ፣ 79 ዓመታት የተረጋገጠ ምልዓት፣ ለአገርትነ-ኢትዮጵያ የቆየ አሻራ ሆኖ የተገለጠ፣ የሻለቃ ጳውሎስ ጌታቸው ናደው ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ ሻለቃን እንቱታውን ሳንዘነጋ፣ ለፍቅራችን ብለን “አንተ” እያልን እንሰኘዋለን፤ አባት አንቱ ስለማይባል፡፡
ከጀነራል ወታደር አባቱ ጌታቸው ናደው ቤተሰብ በረከት ሆኖ የተከሰተው ብርሃናማው መሀንዲስ፣ የኢትዮጵያን ምድር የተቀላቀለው በሀምሌ 5/1938 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሲሆን፣ ልዩ ስሙ ገዳም ሰፈር በተባለ ቦታ ነው፡፡ የአዲስ አበባን ሰማይ ሳይለቅ፣ በቅርብ ርቀት በምትገኘው የምዕራብ ሸዋ ከተማ አንዷ በሆነችው ሆለታ ገነት፣ ከ1 እስከ 4ኛ ክፍል ያለውን የመጀመሪያ መጀመሪያ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ ሕይወት በዝውውር አገሩን እንዲያውቅ ባመቻቸችለት ዕጣ ፈንታም፣ ጉዞውን ወደምስራቃዊቷ የአገራችን ክፍል አቅንቶ፣ ሀረርን የተዋወቃት፣ ከ4ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ያለውን ትምህርት፣ በሀረር ሞዴል ት/ቤት በቆየባቸው ግዚያት ነው፡፡ የወታደር ሕይወቱና ኑሮው በጉዞ የተሞላ፣ በዝውውር የታጀበ ነበርና፣ ከወላጆቹ ጋር ሆኖ የተሰናበታትን አዲስ አበባ፣ በድጋሚ ተዋህዷት፣ ከ6ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን መለስተኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአቃቂ ሚሽነሪ ት/ቤት በጥሩ ሁኔታ አጠናቀቀ፡፡
ብርሃናማው መሀንዲስ፣ ባለብዙ ገፅ የታሪክ ሰው ጳውሎስ ጌታቸው ናደው፣ የአባቱን ጀነራል ጌታቸው ናደውን ፈለግ ለመከተል ያመነታ አይመስልም፡፡ ይህንኑ እውን ለማድረግ፣ በቀና ልቦና እና አገሩን በቆፍጣና ድሲሰፕሊን ለማገልገል ህልሙ ወደነበረው ውትድርና ተቀላቀለ፡፡ በወታደራዊ ምህንድስና ትምህርት ተግቶ፣ በዲፕሎማ ተመርቅ፣ የአገሪቱን የሚሊተሪ ኢነጂነሪንግ ዋልታዋ ሆነ፡፡ በዚህ የሙያ ዘርፍ አንቱታን መቀናጀት ብቻ ሳይሆን፣ እስከአሁንም ድረስ በትልቅ ልማትና ግልጋሎት በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችሉ ተጨባጭ ማሳያ ስራዎችን የከወነ ብርቱ መሃንዲስ ነበር።
በብዙዎቹ የአገሪቷ የወታደራዊ እዝ ውስጥ ያገለገለው ይህ ጀግና ወታደር፣ ዘርዝረን ከማንጨርሳቸው፣ ግን ብንጨልፋቸው መልካም የሆኑ ስራዎቹን እንደሚከተለው እንዘረዝራለን፡-
1. በእድገት በህብረት ዘመቻ፣ የዴስክ እስባባሪ በመሆን ሰርቷል፤
2. በሀረር ወታደራዊ አካዳሚ በአሰልጣኝነት አገልግሏል፤
3. አባቱ ጀነራል ጌታቸው ናደው ሲመሩት በነበረው፣ በሶስተኛው አንበሳው ምስራቅ ክፍለ ጦር በአመራርነት ሰርቷል፤ (ይህም፣ የቀድሞው የኢህዲሪ ፕሬዝደንት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም የነበሩበት) መሆኑ ልብ ይሏል፤
4. ገላዲን በሚባል የ9ኛ ኮማንዶ ሻለቃ የመቶ መሪ በመሆን እና በትግል እስከመቁሰል ድረስ አገልግሏል፤
5. በካራማራ ላይ የተተከለው ራዳር ወደፍፃሜ እንዲደርስ የመሀንዲስነት ሃላፊነት ወስዶ በትጋት ተወጥቷል፤
6. ለ6 ዓመታት በግፍ ከታሰረ በኋላ፣ “ከዘመኑ እንጂ ከአገሬ ጠብ የለኝም፤” በማለት፣ ወደደቡብ እዝ ተመድቦ፣ በእዙ ውስጥ በምህንድስና አዛዥነት አገልግሏል፤ ከሀዋሳ ጋርም የተዋወቀው በዚሁ የስራ ዘመን ውስጥ ነበር፡፡
7. ብሔራዊ የውትድርና ጣብያዎችን በማቋቋም ስራ ውስጥ፣ በተለይ በመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት (መኮድ) ከፍተኛ የምህድንድስናው ድርሻ በመውሰድ፣ ከጀነራል ደምሴ ጎሹ ጋር በጦላይ፣ በደዴሳ፣ ብላቴ፣ ሁርሶና ሌሎችንም በማስገንባት ታላቅ አስተወፅዖ የተወጣ ነው፡፡
8. የጋምቤላ እና ሌሎቹ በደቡብ የአገሪቷ ክፍል ውስጥ የሚገኙ አየር ማረፊያዎችን በማነፅ እና ለስራ በማብቃት የእጁን ጥበብ ያስመሰከረ ብርቱ ወታደር፣ ጳውሎስ ጌታቸው ነው።
9. የኦሞራቴን የጥጥ እርሻ በማጥናትና ፕሮጀክት በመስራት፣ በአገሪቷ ትልቁ ከሚባሉት የመካናይዝ እርሻን ለማስተዋወቅ የበቃ ባለሟል፣ ጳውሎስ ጌታቸው የሰኛል፤
10. በሀዋሳ ከተማ ውስጥ በርካታ ሕንፃዎች ዲዛየን በማርቀቅ፣ ከወታደራዊው ምህንድስና በተጨማሪ፣ በሲቪል ምህድስናው አሻራውን በኩራ አስቀምጧል፡፡ ሁሴን የገብያ አዳርሻ ለማሳያነት ይጠቀሳል፡፡
11. በሀዋሳ የክልሉ ማረሚያ ቤት ውስጥ፣ ቤተ-መፅሐፍት ለታራሚዎች እንዲገነባ በመቀስቀስ፣ ዲዛይን በመስራትና በሺህ የሚቆጠሩ መፅፍትን በማሰባሰብ የለገሰ፣ ታራሚ ወገኖቹን ያፅናና ድንቅ ጀግና ነበር፤
12. በሰራዊቱ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ፣ የአገር ፍቅርና ክብርን፣ ስርዓትና መርሕን አስታኮ፣ በተለያዩ ጋዜጦች በግሩም ፅሑፍ የሚሳተፍ፣ ድካም የማያውቀው ጀግና ሰው፣ ጳውሎስ ጌታቸው ናደው፤
13. በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ሰፊ ጥናት ያደረገ፣ የሞገተ፣ ሶስት ባለትልልቅ ደርዝ መፅሐፍትን የፃፈ፤ ሁለቱ ታትመው ለአንባብያን የደረሱ፣ እንዱ በሕትመት ያለ፣ አራተኛውም በረቂቅ ስራ ተጠናቆ የሚገኝ ነው፡፡ በተለይ “የምርጥ የአበሻ ጀግኖች ታሪክ” ሁለቱም ቅፆች ከ500 ገፅ በላይ መሰናዳታቸው ብቻ ሳይሆን፣ የተዘነጉ፣ ሌላው የታሪክ ገፅ ያላያቸው ኢትዮጵያውያን አርበኞችን ከነገድላቸው የያዘ በመሆኑ፣ ለታሪክ ምልዓት የሚጫወተው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡
14. ሻለቃ ጳውሎስ፣ ከሰራው ጀብድ ውስጥ በብዙዎች የተመሰከረለት፣ “የደርግ መንግስት ከስልጣን በወረደበት ሰሞን፣ እጁ ላይ የነበረውን ከ500 ሺህ ብር በላይ፣ ከነሽራፊ ሳንቲሟ ወደመንግስት ካዝና ያለማንም ጠያቂ የመለሰባት ታሪክ ናት፡፡” ጥቂት የማይባሉ፣ አገር በሸጡበት ማግስት፣ ይህንን ውለታ በታማኝነት መከወን፣ “ከጀብደኝነት” ያነሰ ስም ልንሰጠው አንችልም፡፡
ሻለቃ ጳውሎስ ጌታቸው፣ በገጠመው የአካል ጉዳት ሳይገደብ፣ ከቤቱ ሳይወጣ በንባብ ዓለምን የዞረ፣ የዳሰሰ፣ የተመራመረ፣ የጠየቀና የተፈላሰፈ ጠሊቅ አንባቢ ነው፡፡ ከምላጭ የሰላ የማስታወስ ችሎታው በማንም የታየ አይመስልም፡፡ እያንድአንዷን ቅንጣት የሕይወት ኑባሬውን ከነቀኗ፣ ያነበባትን ከነገፅዋ፣ ያገኛቸውን ሰዎች ከነአያቶቻቸው የሚስታውስ ድንቅ ሰው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሰው፣ እንግሊዞቹ “The Iron Board” ይሉታል፤ አንዴ ከያዘ የማይለቅ አዕምሮ፡፡
በትግል ውስጥ ያለን መታገል፣ ወደመታደል ዕድል መለወጥ ያቻለው ሻለቃ ጳውሎስ፣ በስራው ለሁላችንም ምሳሌ መሆኑ፣ ታሪኩ ድንበርና ዘመን መሻገሩ፣ ጉልህ ትዝታ ያደርገዋል፡፡
ሻላቃ ጳውሎስ ጨዋታ ይችላል፡፡ ማንም አራት ሰዓታት አጠገቡ ሲቀመጥ፣ የአራት አመታት ኮርስ ወስዶ ይሔዳል፡፡ ታሪክ አዋቂ፣ ሳይንስ ተንታኝ፣ የማሕበራዊ እሴት መዝገብ፣ የአገር ፍቅርና ባሕል ቀናዒ ሰው ነው፡፡ በተለያዩ በአገቷ ታላላቅ ሚዲያዎች ላይ የሰጣቸው ቃለ-ምልልሶች፣ ትንተናዎች፣ በተጋበዘባቸው መድረኮች ላይ የሚያደርጋቸው ንግግሮች፣ ዲስኩሮች፣ ለሻይ በመኖሪያ ቤቱ ጠርቷችሁ የሚያነሳቸው ርዕሰ-ነገሮች፣ ለዚህ መገለጫው ከበቂ በላይ ምስክሮች ናቸው፡፡ ሻለቃ ጳውሎስ ጌታቸው ብዙ ሕለሞች ነበሩት፤ በተለይም መፅሐፍትን በማሳተም ዙሪያ፡፡ “120 ዓመት ኖሬ ብዙ መፅሐፍት እሰጣችኋለው፤” ብሎን ያውቃል፤ ሞት ባይቀድመው፡፡ የፈጣሪን ፈቃድ አመስግኖ ከመቀበል ውጭ፣ ምን እንላለን!
ደግ ሰው ጳውሎስ፣ የታሪክ ሊቁ ጳውሎስ፣ መሃንዲሱ ጳውሎስ፣ የአደባባይ ሰው ጳውሎስ፣ ገላጩ ጳውሎስ፣ የእነቅድስት፣ የእነምስራቅ፣ የእነአቤል፣ የእነየማርያም አባት ጳውሎስ ጌታቸው፣ ከወ/ሮ ሮማን አድማሱ ጋር በጥር 1968 ዓ.ም. ተጋብተው፣ ፍሬአቸውን ፈጣሪ የባረከላቸው ጥንዶች ነበሩ፡፡
ሻለቃ ጳውሎስ ከዛሬ በኋላ አያስቸግረንም፡፡ ዛሬ ሰርጉ ነው፤ የመጨረሻው ስንብቱ ነው፡፡ እኛም የምናውቀውን እንመሰክራለን፡፡
ሻለቃ ጳውሎስ በተወለደ በ79፣ ዓመቱ፣ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ፣ ሰኞ ሀምሌ 21/2017 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም አርፏል፡፡
ፈጣሪ ነፍስህን በደጋጎቹ አባቶቻችን አብርሃምና ይስሃቅ ጋራ በቀኙ ያቁምህ!
ለቤተሰቡ፣ ለወዳጅ ቤተ-ዘመድ፣ ለስራ ባልደረቦቹ፣ ለልጆቹ ፈጣሪ ፅናቱን ያድልልን!
2025-07-29