blog post

በግሎባል ፒስ ባንክ አዘጋጅነት “የመደመር መንግስት” መፅሐፍ ለውይይት ቀረበ

11/02/2017 ዓ.ም 

#ሀዋሳ፣ ኢትዮጵያ

በግሎባል ፒስ ባንክ አዘጋጅነት “የመደመር መንግስት” መፅሐፍ ትናንት ሰኞ ጥቅት 10/ 2017 ዓ.ም. ለውይይት ቀረበ፡፡ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) ተፅፎ ለሕትመትና ስርጭት የበቃው “የመደመር መንግስት” መፅሐፍ  ከአንድ ወር በፊት 100 ኮፒዎችን በመግዛት ለ4 ዩኒቨርሲቲዎች እና ለአንባብያን በመግዛት በስጦታ ያቀረበው ግሎባል ፒስ ባንክ በጎ አድራጎት ድርጅት፣ በያዘው ቀጠሮ መሰረት የባንኩ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና አንባብያን በተገኙበት በፅሕፈት ቤቱ በተዘጋጀው መርሃ-ግብር ላይ ለውይይት ቀርቧል፡፡

የግሎባል ፒስ ባንክ ስራ አስኪያጅ አቶ አርጋው አየለ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት፣ “መፅፍትን የመግዛትና የማዳረስ ዋናው ተልዕኮ ከመፅሐፍቱ የሚገኙ ጠቃሚና አገርን ለማቅናት የሚረዱ ሀሳቦችን መውሰድ፣ እውቀትን ማስፋፋት፣ መረጃን መቀባበልና የጋራ አገራዊ መግባባቶች እነዲፈጠሩ ማስቻል ሲሆን፣ የሚገኙ እውቀቶችን መዝኖ፣ ለፖሊሲና ዘላቂ የልማት ዕቅድ እንዲውሉ አማራጭ መንገዶችን ለመፈለግ ይረዳል፤” ብለዋል፡፡

“ይህ አይነቱ ልምመድ በተበታተነ ደረጃ ያለውን የዕውቀት ክምችት ወደአንድ ቋት በማምጣት ለምንገነባው ዲሞክራሲ፣ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ምልዓት የሚረዳ ነው፤” ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ “በዚህ መፅሐፍ የተጀመረው የውይይትና የክርክር ልምምድ ወደ ባሕል ተቀይሮ በሰፊው ልንሰራበት የሚገባ ይሆናል፤” ሲሉ በቀጣይ ለውይይት ስለሚቀርቡ መፅፍት ጥቆማ በመስጠት ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ረዘም ያለ የዝግጅት ጊዜ በመውሰድና በማንበብ የመፅሐፉን ይዘት የዳሰሱት እውቁ የፖለቲካና የዓለም-አቀፍ ግንኙነት ባለሞያው አቶ ደያሞ ዳሌ፣ በዝርዝር የተካተቱ የመፅፉን ርዕሰ-ጉዳዮች ካነሱ በኋላ፣ በተመረጡ ጭብጦች ዙሪያ ለውይይት የሚሆኑ አንኳር ነጥቦችን በማንሳት፣ ከሌሎች የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የማሕበራዊ እና አኮኖሚያዊ ሀልዮት ጋር እያናፀሩ በመተንተን በውይይቱ ወቅት አቅርበዋል፡፡ ከነባር የኢትዮጵያ የሕይወትና ነባራዊ አውድ ጋር ያለውን ግንኙነት በመዳሰስ፣ መፅፉ በዋና አገራዊ የልማት ችግሮቻችን፣ የፖለቲካ ውጥረቶችን፣ በልማት ወደኋላ የመቅረት ምክንያቶች በሰፊው ዳስዋል፡፡  

በመፅሐፉ ይዘት የተካተቱ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰውና የቲክኖሎጂ ደረጃን በማሳያነት አቅርበው፣ ዓለም ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ጋር በየዘርፉ ያሉ ዜጎች መውሰድ ስለሚገባቸው የመፍትሄ እርምጃዎች እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚና እድገት እንዴት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅ የሚያትተውን ይዘት በአፅኖት አተኩረው በውይይቱ ወቅት አቅርበዋል፡፡ በተለይም በፖለቲካ አንድነትና በአንድ ማሕበረ-ኢኮኖሚ ውስጥ የነቃ ማሕበረ-ሰብ መፍጠር ለጋራ መግባባቶችና ርዕይ መዳረሻ ወሳኝ ስለመሆኑ የተተኮረበትን ክፍል፣ አሁናዊ የአገሪቷን ገፅታ በመዳሰስ እና በማመሳከር አቅርበዋል፡፡

በመፅሐፍ ዳሰሳው ላይ የተገኙት ተሳታፊያን እና የሰላም ባንኩ አባላት፣ በመፅሐፉ ዝግጅትና ባነሷቸው ነጥቦች አድናቆታቸውን ገልፀው፣  በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ጥያቄ በማንሳት፣ ሀሳብ በመስጠት፣ ሊካተቱ ይገባቸው ነበር ያሉትን ይዘቶች በማሳያነት በመጠቆም ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ አንድ የአገር መሪ በዚህ ደረጃ ተጨባጭ ችግሮችን ለመፍትሄ ማቅረብና ለሕዝብ ውይይት ክፍት ማድረግ መለመድ እንዳለበት የጠቆሙት ተሳታፊያኑ፣ ይሀ ዓይነቱ ልምደ ቢጎለብት፣ በመንግስትና ዜጎች መካከል የደበዘዘውን የመተማመን ክፍተት ለመሙላት የራሱን ጉልህ ሚና እንደሚጫወትና ዜጎች ያለስጋት በመንግስት እቅድ ውስጥ እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ያስችላል በማለት ሃሳበቸውን አጋርተዋል፡፡ 

ውይይቱ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር መልሰው ደጀኔ አማካኝነት የተመራ ሲሆን፣ የቀጣይ ውይይት ዝግጅት በማስተዋወቅ የመርሃ-ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል፡፡         

2025-10-21