blog post

የግሎባል ፒስ ባንክ መስራች አቶ አርጋው አየለ የእውቅና እና ምስጋና ሽልማት ወሰዱ።

 

ትናንት የካቲት 9/2017 ዓ.ም. በሀዋሳ ኬር አውድ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው የሁለተኛው የደራስያን፣ ጋዜጠኞችና የኪነ-ጥበብ ባለሟሎች የምስጋና እና የእውቅና ስነ-ስርዓት ላይ ነው እውቅናው የተሰጣቸው። ዝግጅቱን ያሰናዳው ሰማይ መልቲ ሚዲያ፣ በስራ አስኪያጁና ባለቤቱ አቶ እዮብ ፅጌ እንደተገለፀው፣  ንባብን ለማበረታታትና ደራስያንን ለማትጋት ታስቦ ላለፉት አምስት ዓመታት "ሀዋሳ ታነባለች" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው መርሃ-ግብር አካል የሆነው 2ኛው ስነ-ስርዓት፣ ካለፈው ተሞክሮ የተሻለውን በመውሰድ፣ ከተለያዩ ተቋማት፣ ባለሃብቶችና የመንግስት አካላት ጋር በማስተሳሰር፣ ንባብና ኪነ-ጥበብን ከሀዋሳ አልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ ማሳደግን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ እነደተገለፀው፣ አቶ አርጋው አየለ፣ ለጀማሪ ፀሃፍያን፣ ለኪነ-ጥበብ ባሞያዎች፣ ለጥበብ ዝግጅቶችና፣ መልካም ስራውች የገንዘብና የቁስ ድጋፍ በማድረግ ባለሞያዎችን የደገፉና ሳይሰለቹ ተከታታይነት ያለው እገዛ ሲያደርጉ የነበሩ በመሆኑ፣ የ2ኛው ዙር የሀዋሳ ታነባለች ዝግጅት ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል። ለተሰጣቸው እውቅናና ሽልማት ምስጋና ያቀረቡት አቶ አርጋው፣ ሽልማቱ ወደፊት ለምንሰራው ስራ ሀላፊነት ከአደራ ጋር የሚጥልብን በመሆኑ፣ ወደፈፊት ሀዋሳ ውስጥ ላሉ ደራስያን የምናደርገው ድጋፍ እንዳለ ሆኖ፣ በቅርብ ጊዜ እቅዳችን ውስጥ፣ ቀድመው ለሚመጡ ለ5 ደራስያን የሕትመት ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ በመድረኩ ላይ አስታውቀዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ፣ ታዋቂው የጥበብ ሰው ደራሱ ሀይሉ ፀጋዬ፣ ገጣሚ በለው ገበየሁ፣ ሻለቃ ጳውሎስ ጌታቸው፣ ጀማሪና አንጋፋ ደራስያን፣ ጋዜጠኞች፣ ባለሀብቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የኪነ-ጥበብ አፍቃሪያን ተገኝተዋል።

2025-02-17